በሴቶችና ሴት ልጆች ላይ የሚፈፀሙ ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃቶችን (VAWG) መከላከል፤ ጥበቃና ምላሽ አሰጣጥ ስርዓት ላይ ያተኮረ የሁለት ቀን ስልጠና በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ  

የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት (ኢ.ሴ.ማ.ቅ) ከዩ. ኤን. ትረስት ፈንድ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ከሰኔ 4-5, 2018 ዓ.ም  በአዲስ አበባ ሳፋየር ሆቴል ለሁለት ቀናት ወሲባዊ እና ሌሎች ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች መከላከል፣ ጥበቃ እና ምላሽ አሰጣጥ ስርዓት ላይ ያተኮረ ስልጠና ከፌደራልና ከክልል ለተወጣጡ የመንግስት ባለድርሻ አካላት ተሰጥቷል።
የኢ.ሴ.ማ.ቅ ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ወ/ሮ ሳባ ገ/መድህን በስልጠናው ቦታ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም ፆታን መሠረት አድርገው የሚፈጸሙ ጥቃቶችን መከላከል፣ከለላ መስጠት እንዲሁም ጥቃቶቹ ተፈጽመው ሲገኙ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጣቸው እንደሚገባ በመግለጽ ለዚህም ደግሞ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እና የተቀናጀ ምላሽ መስጠት እንደሚገባን ገልጸዋል፡፡
በንግግራቸው አክለውም የብሔራዊ የሴቶች ማብቃት እና ስርዓተ ፆታ እኩልነት ፓሊሲ በሚኒስቴሮች ምክርቤት መፅደቁ ለምናከናውናቸው ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች መከላከል፣ ጥበቃ እና ምላሽ አሰጣጥ ላይ ጉልህ አስተዋዕፆ አንደሚኖረው ግልፀዋል፡፡

በስልጠናው ወቅት ተሳታፊዎች ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች መከላከል፣ ከጉዳት በማገገም ላይ ያሉ ሴቶችና ሴት ልጆች ጥበቃ፣ የሪፈራል ስርዓት ማጠናከር እና በተቀናጀ መልኩ ምላሽ ስለመስጠት ግንዛቤ ጨብጠዋል። ስልጠናው በተለይም ግጭት በነበርባቸው እና እሁንም ግጭት ባለባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ውስጥ ለሚገኙ ሴቶች እና ሴት ልጆች የሚደረገው ጥበቃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ የሚሰጡ ምላሾችም በወጡት መመሪያዎች መሰረት መሆን እንዳለበት፣ ምላሽ በመስጠት ሂደት ውቅትም ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶች እና ሴት ልጆችን ማዕከል ያደረገ መሆን እንዳለበት ተገልጿል፡፡
ከአሰልጣኝ ገለጻ በተጨማሪም ተግባራዊ ልምምዶች እና የልምድ ልውውጦችን ተካተውበታል፤ ተሳታፊዎች በየአካባቢያቸው ያሉትን ተግዳሮቶችና መልካም ተሞክሮዎችን በማካፈል ጥሩ የሆነ የእርስ በእርስ መማማሪያ መድረክ ተፈጥሯል፡፡

በመጨረሻም ተሳታፊዎቹ ያገኙትን እውቀት በተቋማቸው ለሚገኘ የስራ ባልደረቦቻቸው ለማካፈል እና የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን ለማጠናከር፣ እንዲሁም ለሴቶችና ሴት ልጆች ተደራሽና ጥራት ያለው አገልግሎት መኖሩን ለማረጋገጥ የተግባር ዕቅድ አዘጋጅተው ለመተግበር ቁርጠኝነታቸውን አሳይተዋል፡፡

ኢ.ሴ.ማ.ቅ እንደ ሁለጊዜው ሁሉ ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች መከላከል፣ ጥበቃ እና ምላሽ አሰጣጥ ስርዓት ለማሻሻል የበኩሏን ድርሻ ትወጣለች፡፡ በተለይም በአማራ፣ ትግራይ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች  ከአጋር ማህበራት እና ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የሴቶችና ሴት ልጆችን መብት፣ ደህንነት እና ፍትህ ለማረጋገጥ  የሚያግዙ ተግባራትን አጠናክራ ትቀጥላለች፡፡
ዓላማችን ለሴቶችና ሴት ልጆች ምቹ የሆነች ኢትዬጵን ማየት ነው፡፡