የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት (ኢ.ሴ.ማ.ቅ) በሴት ልጅ ግርዛት እና ያለዕድሜ ጋብቻ ለማስቆም የማህበረሰብ ንቅናቄና ዘመቻ አካሄደች

በ2018 ዓ.ም. ሐምሌ 15 ቀን፣ በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ በተካሄደው የማህበረሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻ ፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት (ኢ.ሴ.ማ.ቅ) ከ አማራ ሴቶች ማህበር ጋር በመተባበር እና በዩኒሴፍ (UNICEF) በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ፣ የሴት ልጅ ግርዛትን እና ያለዕድሜ ጋብቻን መከላከል ላይ ያተኮረ የማህበረሰብ ንቅናቄና ዘመቻ አካሄዳች።
ዘመቻው የሀገሪቱን ህጎችና ፖሊሲዎች ከማህበረሰቡ አመለካከትና ባህላዊ ልማዶች ጋር በማገናኘት ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶችን ከሥሩ ለመቀየር ያለመ ነበር። ብዙ ሰዎች በሚገኙበት የገበያ ስፍራና የመተላለፊያ አካባቢዎች የተካሄደ ሲሆን ከ3,000 በላይ በስፍራው የተገኙ ገበሬዎች፣ ነጋዴዎች ፤ ህጻናት ፤ እናቶች እና የደባርቅ ከተማና የአካባቢው ነዋሪዎችን በቀጥታ ለማድረስ ተችሏል።
በዘመቻው ውስጥ የደባርቅ ወረዳ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት እና ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት በሚደግፉት ዋልያ የባህል ቡድን አባላት በድራማ፣ በግጥም እና በዘፈን የሴት ልጅ ግርዛትን ፣ ያለዕድሜ ጋብቻን እና ሌሎች ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶችን በጤና፣ በትምህርት፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ ህይወት ላይ የሚያስከትሉትን ጉዳት በሚዳስስ መልኩ አስተማሪ አዝናኝ በሆነ መንገድ አቅርበዋል።
በመዝጊያው የማህበረሰብ ንቅናቄና ዘመቻ ላይ ከህፃናት ጋብቻ የተረፉ ህፃናት የህይወት ተሞክሮዎቻቸውን በማካፈል ተሳትፈዋል። በተጨማሪም የሃይማኖት መሪዎችና የሃገር ሽማግሌዎች የሴት ልጅ ግርዛትና ያለዕድሜ ጋብቻ ከሃይማኖትም ሆነ ከባህል ጋር የማይያያዙ ጎጂ ድርጊቶች መሆናቸውን በይፋ በማረጋገጥ አቋማቸውን ገልጸዋል።
የተቀናጀ የተቋማት ትብብርና ጥበቃ ዘመቻው የህዝብ ተሳትፎን ከማሳደግ ባለፈ፣ ከኢ.ሴ.ማ.ቅ ፣ ከአማራ ሴቶች ማህበር ፤ ከወረዳ ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት፣ በክልል፣ በዞንና በወረዳ ደረጃ ያሉ አመራሮች እንዲሁም ከአካባቢ የዋች ዶግ (ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶችን ተከላካይ ኮሚቴዎች) የተውጣጣ የተቀናጀ የክትትልና የቁጥጥር ቡድን አሳትፏል።
 
የገበያ ቦታው ላይ የተሳታፊዎችን ደህንነት፣ የዘመቻውን ሰላማዊ አፈጻጸም ለማረጋገጥ በወረዳው የተመደቡ አራት የፀጥታ አባላት በሙሉ ጊዜ ጥበቃ አድርገዋል። ይህ የተቀናጀ ተሳትፎ በማህበረሰቡ ውስጥ የሪፖርት ስርዓቶችን በማጠናከር፣ በጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች፣ በማህበረሰብ ፖሊስና በሌሎች ተቋማት መካከል ያለውን ቅንጅት በይበልጥ አጠናክሮል። እንዲሁም ለፆታዊ ጥቃት ተጎጂዎች የሚገኙ የሪፈራል አገልግሎቶችን በተመለከተ ግልጽ መረጃ ለህዝቡ ተሰጥቷል።
በተጨማሪም በአካባቢው ቋንቋና አውድ የተዘጋጁ በራሪ ወረቀቶች ለህዝቡ ተሰራጭተዋል። እንዲሁም በዘመቻው የአካባቢ የዋች-ዶግ መዋቅሮች የበለጠ ተጠናክረው የሴቶችና የህጻናት መብትና የአካል ደህንነትን ለመጠበቅ የተቋማት እና የማህበረሰቡ የጋራ ቁርጠኝነት የታየበት ነበር።
በነበረው የማህበረሰብ ንቅናቄ ዘመቻም በቀጥታ መረጃውን ከተካፈሉት ማህበረሰብ አባላት በተጨማሪ በተበተኑት በራሪ ወረቀቶች ፤ በተለያዩ ማህበራዊ ሚድያዎች ፤ ቲሸርቶች ፤ በተያዙ መፈክሮች አማካኝነት ከ 15,000 በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ተደራሽ ይሆናል፡፡