"ጥምረት ለሴቶች ድምፅ" የሴቶችን አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ አስረከበ።
ሀምሌ 18/2016 ዓ.ም
ጥምረት ለሴቶች ድምፅ፤ በስምንት ክልሎችና በሁለት ከተማ አተስተዳደሮች ያሰባሰባቸውን የሴቶችን አጀንዳዎች ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረክቧል።የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች የጥምረቱን አጀንዳዎች ከጥምረቱ አመራሮች ተረክበዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መሥፍን አርአያ (ፕሮፌሰር) ፤ ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ በአሠራር ሥርዓቱ አካትቶ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።
ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ የሴቶችን ግንዛቤና ተሳትፎ ለማሳደግ ያደረገው ጥረት የሚያስመሰግን መሆኑንም ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። ኮሚሽኑ የተሰበሰቡትን የሴቶች አጀንዳዎች በሀገራዊ የምክክሩ ላይ እንደሚጠቀማቸውም አስታውቀዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የሴቶች ጉልህ ተሳትፎ የሌለበት ሀገራዊ ምክክር ሙሉ እንደማይሆን ገልፀው፤ የተሰበሰቡት አጀንዳዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የጥምረት ለሴቶች ድምፅ ሰብሳቢ ሳባ ገብረመድህን፤ ጥምረቱ በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።ጥምረቱ ከኮሚሽኑ ጋር በቅርበት ሲሠራ መቆየቱን ገልጸው፤ በክልልና በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ የሴቶች አደረጃጀቶች በቀጣይ ጊዜያት በምክክሩ ላይ በጋራ እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።
ጥምረት ለሴቶች ድምፅ ሀምሳ አምስት የሴቶች ማህበራትን ያቀፈ ድርጅት ነው፡፡

Share this post: on Twitter on Facebook on LinkedIn